Wednesday, October 4, 2017

ስለ እመቤታችን ትንቢት እና ምሳሌ

ስለ እመቤታችን ትንቢት እና ምሳሌ
፩. ዳግሚት ሔዋን፦
"በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትነክሳለህ።" ዘፍ ፫፦፩፡፲፭
መፍቀሬ ሰብዕ የሆነው አምላክ በምክረ ከይሲ ተታለው በኃጢአት ተሰናክለው በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት ይጠቀጠቁ ለነበሩት ለአባታችን አዳምና ለእናታችን ሔዋን እንዲሁም ለልጆቻቸው የተሰጠ አምላካዊ የተስፋ ቃል ነው።
ታዲያ የዚህ ትንቢት ቃል ፍጻሜ በማን ነበር ቢሉ በወላዲተ አምላክ በድንግል ማርያም ነው።
መጽሐፍም፦ "ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፤
                      ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል።"
ትርጓሜውም፦ የቅዱሳን አበው ተስፋ ድኅነት በቅድስት ድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ የድኅነተ ዓለም ሥራ የተፈጸመበት መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ።
ራዕ ፲፪፦፲፯ በአዲሲቱ (ዳግሚት) ሔዋንና በዲያብሎስ መካከል ያለውን ጸብና ክርክር ያሳያል።
አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥክ። መዝ ፳፫፦፲፬ ፣ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። መዝ ፲፩፦፲፮ የሚሉት ጥቅሶች ከላይ ለተጠቀሰው ፍጻሜ ማግኘቱን ያረጋግጣል። 
ዮሐ ፳፫፦፲፬ ፣ ፴፬፣ ፳፦፳፭ ዲያብሎስ በአይሁድ ልቦና አድሮ ክርስቶስን እንደቸነከሩት ያስረዳል።
ገላ ፬፦፬፡፭ ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ፤ ከሴትም ተወለደ። እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ።
ይህ የድኅነት ቃል  በቅድስት ድንግል ማርያም መፈጸሙን ማስተዋል ይገባል።
*የመጀመርያውን ተአምር ባደረገበት በገሊላ ቃና ሰርግ ቤት ፤ ዮሐ ፪፦፬ ፣ እዲሁም በቀራንዮ መስቀል ላይ ሳለ ዮሐ ፲፱፦፳፮ *አንቺ ሴት* ሲል መጥራቱ አስቀድሞ ለሰው ልጆች የሰጠው የተስፋ ቃል ኪዳን በርሷ በኩል መፈጸሙን በምስጢር ያስረዳል።
ቀዳሚት ሔዋን ባለመታዘዟና  ባለመታመኗ ሞትን  በርሷ ምክንያት ለሰው ልጆች ስታመጣ ዳግሚት ሔዋን የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ለፈጣሪዋ ፈቃድ በመታመኗና በመታዘዟ ምክንያት በሞት ጥላ ስር ወድቆ ለነበረው የሰው ዘር በረከትንና ሕይወትን አስገኘች።
=> "የሔዋን ጠበቃ አለኝታ ***ቅድስት ድንግል ማርያም። "
ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ፩ኛ ዮሐ ፫፦፰
፪. ሐመረ ኖህ (የኖህ መርከብ)
ከላይ እንደተገለጠው  የሰው ልጆች ርግማን በቀዳሚት ሔዋን በኩል ቢመጣም መፍቀሬ ሰብዕ የሆነው አምላክ ቃሉን ባለመጠበቃቸው ቢፈርድባቸውም ፤ ቅጣቱን እነሱ ሊከፍሉት ስለማይችሉ ከሴት ተወልዶ እንደሚያድናቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ቃሉን የማያጥፈው አምላክ ጊዜው ሲደርስ ሰው ሆኖ እንደሚገለጥ ቢነግራቸውም  ሰው ናቸውና ተስፋ እንዳይቆርጡ የጨለማውን ዘመናቸውን በምሳሌ እና በሕብር  ሲያጠነክርላቸው መቆየቱን ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክራችን ነው። ከነዚህም ምሳሌዎች ውስጥ የኖህ መርከብ በድንግል ማርያም ተመስላ መቅረቧ ነው።
ኖህ በዘመኑ ሰብዓ ትካት ከሕገ እግዚአብሔር ወጥተው በማይገባ የበደልና የኃጢአት ዓለም ውስጥ መገኘታቸው በንፍር ውሃ (በውሃ ጥፋት) የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው ላይ ነደደባቸው። ይሁን እንጂ ይህ ጻዲቅ በፈቃደ እግዚአብሔር ይመራ ስለነበር ከዚህ አስፈሪ ቅጣትና ቁጣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተግቶና ነቅቶ በሰራት ባለ ሦስት ክፍል መርከብ ከጥፋት ውሃ ድኗል። ዘፍ ፮፦፲፬፡፰፦፲፱ ዕብ ፲፩፦፯
ሐመረ ኖህ =ከቁጣው ሸሽተው የተደበቁባት ከመጥፋት የዳኑባት ስትሆን እ ግዚአብሔር በቸርነቱ ጠብቆ ያኖራት የተጠለሉባትን ነፍሳት ይዛ ከፍ ከፍ ያደረጋት ነች።
ሐመረ ኖህ => የእመቤታችን ምሳሌ፤
ጻዲቁ ኖህ  => የመድኃኒታችን የክርስቶስ ምሳሌ፤
ኖህ ወደ መርከቢቱ መግባቱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማህጸነ ድንግል የማደሩ ምሳሌ ነው። 
ሐመረ ኖህ ባለ ሦስት ክፍል መሆንዋ እመቤታችን በሦስት ወገን ንጽህት እንደሆነች ለማጠየቅ ነው ፤ ማለትም ንጽሐ ሥጋ ፣ ንጽሐ ነፍስ ፣ ንጽሐ ልቡና ያጌጠችና የከበረች አንድም በሐልዮ ፣ በነቢብ ፣ በገቢር አንድም በሦስቱ ድንግልናዋ ቅድመ ጸኒስ ፣ ጊዜ  ጸኒስ ፣ ድኅረ ጸኒስ ዳግመኛም ቅድመ ወሊድ ፣ ጊዜ ወሊድ ፣ ድኅረ ወሊድ ዘላለማዊ ድንግል መሆንዋን ያሳያል።
*እውነተኛ ሠላማዊት የኖህ ርግብ፤ዘፍ፰፦፰፡፲፪
*ሐመረ መድኃኒት (የመድኃኒት መርከብ)  ናት።
 

አንባቢ አስተውል!!!  እግዚአብሔር የመረጣት እውነተኛ መርከብ ኃጢአታችን ሲበዛከ ጥፋት እንድንባት (እንጠለልባት) ዘንድ የተሰጠችን ቅድስት ድንግል ማርያም ነች። የጥፋት ውሃ ሲመጣ ወደ መርከቢቱ ግቡ ሲባሉ እምቢ ያሉት አመጸኞች የመጨረሻው እጣ ፋንታቸው ከምድረ ገጽ መጥፋት እንደሆነው ሁሉ በድንግል አማላጅነት አንጠለልም የምትሉት የዛሬዎቹ አመጸኖች ደግሞ  የመጨረሻው እጣ ፋንታችሁ ከርስት መንግሥተ ሰማያት መጥፋት ነው። ይህም እግዚአብሔር በፈቃዱ ለዓለም መዳኛ ምክንያት ላደረጋት ከፍጥረታት ሁሉመርጦ የከተመባት የንጉሥ ከተማ አማላጅነት ከማመን መውጣት የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ መቃወም ነው። አልሰማሁም ሳላውቅ ነው ማለት አያድንም የእግዚአብሔር ድንቅ ስጦታ እንጠለልባት ዘንድ የተሰጠችን አማናዊት መርከብ ቅድስት ድንግል ማርያም ነች። ይህንንም ሐዋርያው ሲያረጋግጥ እንዲህ ነበር ያለው፦ እግዚአብሔር ያጸደቃቸውን ማን ይከሳቸዋል? እንግዲህ እናስተውል!! እኛ ኦርቶዶክሳውያን ሳንሆን ራሱ ፈጣሪ " አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተለየሽ ነሽ ደስ ይበልሽ!!! ያላትን እኛ የምናጣጥላት ከሆነ ከሳሾች እንሆን ዘንድ እኛ  ማንነን ልንል ይገባል።

፫. ሰዋስወ ያዕቆብ (የያዕቆብ መሰላል)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአካላዊ ቃል ርደት ፣ ለሥጋ እርገት ምክንያት  በመሆኗ ያዕቆብ ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ በላይዋ ላይ ዙፋን ተጭኖባት በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት ፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት በፍኖተ ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል ነች (ትመሰላለች)።ዘፍ፰፦፲፡፲፮

=>እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመሰላሏ ትመሰላለች፤

=>ያዕቆብ ተንተርሶት የነበረው ድንጋይ በትንቢተ ነቢያት ይመሰላል።

=>ይህም የሕይወት መሰላል ወላዲተ አምላክ መሆንዋን በግልጽ ያመሰጥራል።

=>የመሰላሏ ጫፍ፦ በመሰላሏ ጫፍ ላይ የነበረው ንጉሥ ሞት ሽረት ፣ በመንግሥቱም ህልፈት ፣ ውላጤ የሌለበት ሰማያዊውና ዘላለማዊው ንጉሥ ፱ ወር ከ፭ ቀን የነገሠባት የማህጸነ ድንግል ምሳሌ ነው።

=>በመሰላሏ አማካኝነት መላእክት ወደ ታች መውረዳቸው አማናዊቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአካላዊ ቃል ርደት ምክንያት መሆንዋን ያመሰጥራል።

=> በአንፃሩ መላእክት በመሰላሏ አማካኝነት ወደ ላይ መውጣትና ማረግ ከክብሩ ተዋርዶና በባህርይውም ጎስቁሎ የነበረው ሥጋ በርደተ ቃለ እግዚአብሔር መክበሩንና በተዋሕዶ መለኮት የባህርይ አምላክ  መሆኑንም በግልጽ ያስረዳል።

“ The Nativity of Christ is the birth day of the whole human race! " አባ ባስልዮስ ዘቂሳርያ
" The son of God become the son of Man so that the son of Man might become the son of God; The son of God become Man so as to deify us in himself. By becoming Man He made us sons to the Father."
ትርጉም፦ ወልደ እግዚአብሔር ወልደ እጓለእመሕያው የሆነው ወልደ እጓለ እመሕያው በጸጋ ውሉደ እግዚአብሔር እንድንሆን ነው። ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ